ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የካበተ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ልምድ በመጋራት ለአህጉራዊ ሰላምና ደኅንነት በጋራ መሥራት ይገባል - አምባሳደር አብዱልፈታህ ሙሳህ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የካበተ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ልምድ በመጋራት ለአህጉራዊ ሰላምና ደኅንነት በጋራ መሥራት እንደሚገባ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር አብዱልፈታህ ሙሳህ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና መንግሥታቸው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በማዘጋጀታቸውም ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በዚሁ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ(ኢኮዋስ) የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር አብዱልፈታህ ሙሳህ(ዶ/ር)፤ የጉባዔው መዘጋጀት ለአህጉራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማበጀት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በአህጉሪቱ የሚስተዋሉ በተለይም የሰላምና ደኅንነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ ግንዛቤና መግባባት የሚፈጠርበት መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ጉባዔውን ማዘጋጀቷ የአፍሪካውያንን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ቀጣናዊ ትብብር እንዲጎለብት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ የምታደርግ ሀገር ናት ያሉት አምባሳደሩ፤ በሶማሊያና በሌሎች ግጭት በሚስተዋልልባቸው የአህጉሪቱ ሥፍራዎች ታላቅ ሚና እየተጫወተች ስለመሆኑም አንስተዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን የካበተ ልምድና ተሞክሮ በመጋራት ለአህገራዊ ሰላምና ደኅንነት የትብብር ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል ብለዋል።

ጉባዔው በዓለም ብሎም በአፍሪካ ሊቢያ፣ ሱዳንና የሳኅል ቀጣና ለአህጉሪቷ ትልቅ የህልውና ስጋት ለመሆኑ ችግሮች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላምና ደኅንነት ስልቶች ለመቀየስ አስፈላጊ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር በሥራ ላይ ያለውን የአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ተጠባባቂ ኃይል አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ጠንካራ አህጉራዊ የጸጥታ ተቋም መገንባት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

አምስቱም የአፍሪካ ቀጣና የየራሳቸው ተጠባባቂ ኃይል መስርተዋል ያሉት አምባሳደር አብዱልፈታህ፤ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመከላከያና የፋይናንስ ሚኒስትሮች ለቀጣናው የሰላም ስጋት ምላሽ የሚሰጥ የፀረ-ሽብር ኃይል በማቋቋም ወደ ሥራ ለማስገባት ምክክር እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

የአህጉሪቱን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይልን በጠንካራ መሠረት ላይ መገንባት የሚያስችል አካሄድ መከተል ይገባል ብለዋል።

አህጉራዊ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በመፍጠር ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርሰውን የአህጉሪቱ ወጣት ኃይል ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የልማት ትስስር መፍጠርም የሀገራቱን ትብብር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በጉባዔው የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ወታደራዊ አታሼዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም