የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ):- የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማኅበር 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ”አንድ ጤና አንድ ዓለም!” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የእንስሳት ኃብት በጥራት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ አንጻር ዘርፉን ለማሳደግና ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማኅበር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በቀጣይም የዘርፉ የሕክምና ባለሙያዎች እንስሳትን ከበሽታዎች በመከላከል ለሀገር እድገት የላቀ አስተዋጽዖ እንዲኖራቸው እገዛቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በመንግሥት በኩል የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ቦጃ እንደቦ(ዶ/ር)፤ የማኅበሩ 50ኛ ዓመት ምሥረታና 37ኛ ዓመታዊ ጉባዔው በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር መጀመሩን ተናግረዋል።
በጉባዔው የእንስሳት ጤና ጋር ተያያዥ የሆኑ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግበትም ገልፀዋል።
በዛሬው መድረክ የእንስሳት ጤና እንዲሻሻልና በዘርፉ ልዩ ልዩ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እውቅና እና ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፤ ጉባዔው ነገም የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።