አዲስ አበባ ውብ፣ ዘመናዊና ምቹ ከተማ ሆና ማየታችን አስደንቆናል- እንግሊዛዊያን ቱሪስቶች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ውብ፣ ዘመናዊና ምቹ ከተማ ሆና ማየታችን አስደንቆናል- እንግሊዛዊያን ቱሪስቶች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ውብና ዘመናዊ ከተማ ሆናለች፤ በከተማዋ ያየነው የኮሪደር ልማትም አስደንቆናል ሲሉ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙ እንግሊዛውያን ጎብኝዎች ገለጹ።
ከጎብኝዎቹ መካከል ማንክ ዊሊያምስ እና አንቶኒ ቺብኑዚ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የነበራቸው ህልም ተሳክቶ አዲስ አበባን በማየታቸው ተደስተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን እየጎበኙ መሆኑን የተናገሩት ዊልያምስ፤ አፋርን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን ድንቅ የኢትዮጵያ የመስህብ ስፍራዎችን ለማየት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ባደረጉት ጉብኝትም የሉሲን አጽም ጨምሮ የተለያዩ የአርኪኦሎጂ ቅርሶችን በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባን ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ጋር ያነጻጸሩት ዊሊያምስ፥ አዲስ አበባ እጅግ እየዘመነች የምትገኝ ውብና አስደናቂ ከተማ ሆና እንዳገኟት ጠቅሰዋል።
በከተማዋ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ ግዙፍና ዘመናዊ ህንጻዎችና የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ከጠበኩት በላይ ውብ ሆነው ነው ያገኘኋቸው ይላሉ።
ይህም ኢትዮጵያ በዘመናዊ ከተማ ግንባታና በቱሪዝም መሠረተ-ልማት ተጨባጭ ለውጥ እያሳየች መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።
የውጭ አገር ጎብኝዎችን በመሳብ የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
ሌላው የእንግሊዛዊ ቱሪስት አንቶኒ ቺብኑዚ በበኩላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች በመልካም ሁኔታ እንግዳ ይቀበላሉ ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ከተማዋ የለመለሙ ዕፅዋት፣ ምቹ አየርና የመዝናኛ ስፍራ ያላት ሆና በማግኘታቸው እንደተደነቁም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ እንደ ቡና አፈላል፣ የምግብ አዘገጃጀትና ሌሎች የማህበረሰቡን ባህላዊ ስርዓቶችን ለማየት እንደጓጉም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የዓለም ቅርስ የሆኑ ታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎችን የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸውም እንዲሁ።