የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ መምህራን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል እየሰራሁ ነው - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ መምህራን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል እየሰራሁ ነው - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

አዳማ ፤ ጥቅምት 7/2017 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ መምህራን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ገለፀ።
37ኛው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክር ቤት ጉባዔ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ባንቲ (ዶ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የመምህራን መብት በተለይም ጥቅማ ጥቅምና የሚያጋጥማቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የሙያ ማህበሩ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም በትምህርት ጥራት መረጋገጥ፣ በየደረጃው የሚካሄደው የማህበሩ ምርጫ፣ መምህራን በሀገራዊ ምክክር በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ እንዲሁም ሰላምን በመጠበቅ ረገድ በሚኖራቸው ሚና ላይ ጉባዔው በጥልቀት ይመክራል ብለዋል።
መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ማህበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ በእስከአሁኑ ሂደት ከ120ሺህ በላይ የሚሆኑ መምህራን በሀገር አቀፍ ደረጃ የመኖሪያ ቤትና ቤት መስሪያ ቦታ ማግኘታቸውን እንደ አብነት አንስተዋል።
በስራ ክብደት ምዘናና ደረጃ ምደባ የመምህራን ደመዋዝ እንዲስተካከልም ባለፉት ዓመታት መሰራቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁንም ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን ነው ያሉት።
መምህርነት የሚኖረው ጥራቱን የጠበቀና የተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ ሲኖር ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የትምህርት ጥራት ችግሮችና ጉድለቶችን የሚለዩ ጥናቶችን በማካሄድ የመፍትሄ ሐሳቦች ለመንግስትና ባለድርሻ አካላት እያቀረቡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተለይ የትምህርት ቤቶች የፋይናንስ ድጋፍ ፈንድ የማሰባሰብና አቅማቸውን የማጎልበት፣ የትምህር መርጃ ቁሳቁስና ተያያዥ ግብዓቶች እንዲሟሉ እንዲሁም ቤተ ሙከራዎች እንዲደራጁ ማህበራቸው ድጋፍ እያደረገ መሆኑንዝም እንዲሁ።
ከጉባዔ ታሳተፊዎች መካከል የኦሮሚያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዋቅወያ ቶሌራ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የመምህራን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት በክልሉ ከሶስት ሺህ በላይ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራት ጉዳይ የማህበሩ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የመብት ጥያቄ ብቻ ማቅረብ ሳይሆን በሙያችን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ እየሰራን ነው ብለዋል።
ከደመዋዝ፣ ከዝውውርና ከደረጃ እድገት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችንም ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን በማንሳት።
በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት በተሰናዳው ጉባዔ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የመምህራን ማህበር አመራር አባላትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጋበዙ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።