በመደመር እሳቤ የተጀመረውን የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሃሳብና የተግባር አንድነት በመፍጠር መሥራት ይገባል- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር እሳቤ የተጀመረውን የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሃሳብና የተግባር አንድነት በመፍጠር መሥራት ይገባል- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦በመደመር እሳቤ የተጀመረውን የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሃሳብና የተግባር አንድነት በመፍጠር መሥራት ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በሀገራዊ ለውጡ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በማጽናት ፈተናዎችን በጋራ ለመሻገር መሥራት ይገባል ብለዋል።
በለውጡ ሂደት በመደመር እሳቤ የተጀመረውን የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሃሳብና የተግባር አንድነት በመፍጠር መሥራት ይገባል ብለዋል።
በለውጡ ሂደት ዘርፈ-ብዙ እመርታዎች እየተመዘገቡ መሆኑን የጠቀሱት አፈ-ጉባዔው ዘላቂ የማድረግ ሥራ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ የምክር ቤት አባላት ከሕግ ማውጣት ጀምሮ አስፈጻሚ አካላትን በመከታተል፣ በመደገፍና በመቆጣጠር የሚኖራቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጸንታ የቆመችው በየጊዜው የገጠሟትን ችግሮች ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ በጋራ በመቆሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የኢኮኖሚ ልዕልናን ለማረጋገጥ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የምክር ቤት አመራርና አባላት ሥልጠና ''የህልም ጉልበት ለእመርታዊ ዕድገት!'' በሚል መሪ ሀሳብ ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።