በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአንድ ዓመት ብቻ ከውጭ የሚገቡ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን መተካት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአንድ ዓመት ብቻ ከውጭ የሚገቡ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን መተካት ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአንድ ዓመት ብቻ ከውጭ የሚገቡ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል፣ ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው።
ንቅናቄው የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ወደማበርከት እየተሸጋገረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ፣ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ሀገራዊ ወጪን መቀነስ ላይም ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ንቅናቄው ባለፈው ዓመት ብቻ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አመልክተዋል።
ለዘርፉ የሚቀርቡ የብድር፣ የውጭ ምንዛሪና የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው፥ በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በተያዘው ዓመትም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ሚኒስትሩ ያረጋገጡት።