የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሪፎርም ሥራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮችና ወታደራዊ አታሼዎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሪፎርም ሥራዎችን ጎበኙ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፥ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የተከናወኑ የለውጥ ስራዎችን በተመለከተ ለጎብኝዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በለውጡ በሰው ኃይል ስልጠና፣ በዘመናዊ ወንጀል መከላከልና ምርመራ፣ በሰላምና ጸጥታ ማስከበር ጠንካራ አቅም መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ2030 ከአፍሪካ አምስት ቀዳሚ የፖሊስ ተቋማት ውስጥ ለመሆን ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በአፍሪካ አህጉራዊና ቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር ትብብርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ፌደራል ፖሊስ ከሀገር አልፎ በአህጉሪቱና በዓለም ሰላምና ጸጥታ በነበረው አስተዋፅኦ እውቅና ማግኘቱን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም