የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ):-የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎበኙ።
ሚኒስትሮቹ በአዲስ አበባ እተካሄደ ከሚገኘው የአፍሪካ የመከላከያ የሚኒስትሮች ጉባኤ ጎን ለጎን ነው የጎበኙት።
ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት እያከናወነች ያለውን ተግባር እና የገነባችውን አቅም በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በፋይናንስ፣ በደህንነት፣ በመሰረተ ልማትና ሌሎች የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ለመመከት የተገነባው አቅምን ጎብኝተዋል።
በተመሳሳይ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የፌደራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን እንደሚጎበኙ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የገነባችውን አቅም የጎበኙ ሲሆን በትላንትናው እለትም የኢትዮጵያ አየር ሃይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ጸጥታና ሰላም”በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሔደው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል።
በጉባኤው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ወታደራዊ አታሼዎችና የዘርፉ ተመራማሪዎች ተሳትፈውበታል።