ቀጥታ፡

ጃፓን የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ሂደት እንደምትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ):- ጃፓን ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።

የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር ተወያይተዋል።

ምክክሩ ኢትዮጵያ እና ጃፓን በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር ሴክሬታሪያት ኃላፊ እና የባለሙያዎች ቡድን አባላት ተገኝተዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመጨረሻ ጊዜ እልባት በመስጠት ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

በፖሊሲው ላይ አሳታፊ እና ግልጽ ውይይት መደረጉን አስታውሰው የፖሊሲው ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ የተመላከቱትን ማስተግበሪያ ስልቶች የሚተገብሩ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች በመዘጋጀት ላይ ናቸው ብለዋል።

የጃፓን መንግስት በሕግ ረቂቆቹ ላይ የሚደረጉት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ጨምሮ በፖሊሲ ትግበራ ፍኖተ ካርታው ላይ የተመላከቱትን ተግባራት በመተግበር ሂደት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል።


 

ኢትዮጵያ እና ጃፓን ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው ይህ ትብብር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚጠቀጥል እምነታቸው መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እና ጠንካራ ወንድማማችነት እንዳላት ገልጸዋል።

ጃፓን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደምትግፍ ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ዴሞክራሲን ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው ሀገራቸው የትግበራ ሂደቱን ለመደገፍ ዝግጁ ናት ብለዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ጃፓን በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ማዕቀፍ ለማዘጋጀት መስማማታቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም