ቀጥታ፡

ከ48 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ታዳጊዎች የተሳተፉበት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ማጠቃለያ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017(ኢዜአ)፦ ከ48 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ታዳጊዎች የተሳተፉበት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር የማጠቃለያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድሩ በአብርሖት ቤተ-መጽሀፍት እና የአፍሪካ ሲልከን ቫሊ ትብብር "አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለበጎ ተጽዕኖ" በሚል መሪ ሃሳብ ሲያካሄድ ቆይቷል።

በዛሬው እለት ደግሞ የማጠቃለያ ስነ ስርአቱ በአድዋ መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ግዙፍ የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ውድድር ከ48 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 4 ሺህ 928 ታዳጊ ወጣቶች ተወዳድረውበታል።

በትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እና በመሳሰሉት ወሳኝ የፈጠራ ስራዎች ለችግሮች መፍትሄ የሚሆኑና ቀልጣፋ አሰራር የሚፈጥሩ ፈጠራዎቻቸውም ለውድድር ቀርበዋል።

በዚህም አገራቸውን በመወከል ምርጥ ሰባት ውስጥ የገቡ የኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ታንዛኒያ፣ አልጀሪያ እና ቱኒዚያ ታዳጊዎች ለመጨረሻው ውድድር ቀርበዋል።

በዛሬው የማጠቃለያ ፕሮግራምም ተወዳዳሪዎቹ እንደየደረጃቸው 30 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት የሚከፋፈሉ ይሆናል።

በማጠቃለያ መርሃግብሩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፣ የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ፣ የአብርሖት ቤተ-መጽሐፍት እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ስራ አስኪያጅ ውባየሁ ማሞ (ኢ/ር) እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም