የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ከጉባኤው በተጓዳኝ የኢትዮጵያን የመከላከያ ተቋማት የካበተ ልምድ እየተጋሩ ነው - ኢንጂነር አይሻ መሃመድ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ከጉባኤው በተጓዳኝ የኢትዮጵያን የመከላከያ ተቋማት የካበተ ልምድ እየተጋሩ ነው - ኢንጂነር አይሻ መሃመድ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ከጉባኤው በተጓዳኝ የኢትዮጵያን የመከላከያ ተቋማት የካበተ ልምድ እየተጋሩ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ተናገሩ።
በመከላከያና የጸጥታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት በርካቶች ፍላጎት ማሳየታቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በዛሬው እለት በቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢትዮጵያ አየር ሃይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጎብኝተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በተገኙበት ሚኒስትሮቹ ተቋማቱን ጎብኝተዋል።
የጉባኤው ዋነኛ አላማ የአፍሪካ አገራት በመከላከያና የጸጥታ ተቋማት ልምድ በመካፈል በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ኢንጂነር አይሻ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሮቹ የጎበኙት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከ80 አመታት በላይ የዘለቀ ልምድ ያካበተ ግዙፍ ተቋም በመሆኑ የተደሰቱበትና ጥሩ ተሞክሮ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከጊዜው ጋር እየዘመነ የላቀ አቅምና ብቃት ያካበተ ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የጉባኤው ተሳታፊዎች በቆይታቸው ከጉባኤው በተጓዳኝ የኢትዮጵያን የመከላከያ ተቋማት የካበተ ልምድ እየተጋሩ ነው ብለዋል።
የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመከላከያና የጸጥታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሮቹ በዛሬ ቆይታቸው የኢትዮጵያ አየር ሃይል እና የመከላከያ ኢንዳስትሪ ኮርፖሬሽንን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።