ቀጥታ፡

በውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለው የምንዛሪ አቅርቦት መሻሻል አሳይቷል - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017(ኢዜአ)፦ በውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለው የምንዛሪ አቅርቦት መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በቅርብ ጊዜ ስራ የጀመሩ ሁለት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (independent forex bureaus) ጎብኝተዋል።

ቢሮዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እና ቦሌ አካባቢ የሚገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ሁለት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ስራ መጀመራቸው መልካም  እንደሆነ ገልጸዋል።

ቢሮዎቹ ለግል እና የቢዝነስ ጉዳይ ወደ ውጭ አገር ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያንን ፍላጎት ለማሟላት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።


 

ከግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ጎን ለጎን በባንኮች የተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የምንዛሪ አቅርቦት መሻሻል እያሳየ መሆኑንም አመልክተዋል።

ማሞ ምህረቱ ሁሉም ባንኮች የደንበኞችን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በፍጥነት እንዲያስተናግዱም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያደገ ያለው ፣ ገበያ መር የሆነው እና ጤናማ ለውጥ እያሳየ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገበያ የኢትዮጵያን ላኪዎች እና አስመጪዎችን ፍላጎት ያረጋገጠ እንዲሆን የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎቹ የስራ ኃላፊዎች ለተጓዦቹ አስፈላጊውን የውጭ ምንዛሪ እያቀረቡ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም