የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ከህዳር ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ ይሸጋገራል - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ከህዳር ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ ይሸጋገራል
ድሬዳዋ ፤ጥቅምት 06/2017(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ከመጪው ህዳር ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መጠናቀቁን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
አገር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራ ኮሚቴ አባላት የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ዛሬ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ተመልክተዋል።
የአመራር አባላቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሚከናወኑ ቅንጅታዊ ስራዎች ላይም መክረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ውይይቱን ተከትሎ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት ተሰርተዋል።
በዚህም የመሠረተ ልማቶች ዝርጋታዎች፣ የጉምሩክ፣ የታክስ፣ የጥቅማጥቅም አሠራሮችና የህግ ማዕቀፎች መጠናቀቃቸውን አረጋግጠዋል።
እነዚህ የቅደመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸው ነፃ የንግድ ቀጠናው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቻ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎቱን የንግድና ሎጂስቲክስ ዘርፎችንም በማካተት ከህዳር ወር ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለማስገባት ያስችለዋል ብለዋል።
እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ መግባት ደግሞ ለውጭና ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ሁሉን አቀፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶች ለመስጠት ያስችላል፤
የወጭና ገቢ ንግድን ያሳልጣል፤ የሎጀስቲክስ ዘርፍን ቀላልና ምቹ ያደርጋልም ብለዋል።
በተለይ የነፃ ንግድ ቀጠናው ወደ ሙሉ አቅም መሸጋገር በጅቡቲ ወደብ ላይ ለሚራገፉ ምርቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የሚወጣን የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚያስችል ነው ያወሱት።
የነፃ ንግድ ቀጠናው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት የሚችለው የፌደራል እና የድሬዳዋ ተቋማት በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ በጋራ በመስራት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዛሬ በድሬዳዋ የተካሄደው የመጨረሻው ጉብኝትና ውይይት ይሄን አገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት እንደሆነም አስረድተዋል።
ዛሬ በተካሄደው የመስክ ጉብኝትና ውይይት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር)፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።