ቀጥታ፡

የቡና ጥራትን በማስጠበቅና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራን ነው

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ):-የቡና ጥራትን በማስጠበቅና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን አምራችና ላኪዎች ተናገሩ።

የጂ-25 ቡና አምራች ሀገራትን በሊቀመንበርነት እየመራች ያለችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ በዓለም ደግሞ ሦስተኛ የቡና አምራች ሀገር መሆኗ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቡና ምርት ባለፉት አምስት ዓመታት በ500 ሺህ ቶን እጥፍ ያደገ ሲሆን፤ ከወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በዘንድሮው ዓመትም ከቡና የወጪ ንግድ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

በቡና ምርት ልማት የተሰማሩ ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የቡና ምርት ልማትና ጥራት በየጊዜው እድገት በማሳየት በተለይም የባለ ልዩ ጣዕም ቡና የገበያ ተፈላጊነት በእጅጉ ጨምሯል። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አምራችና ላኪዎች የቡና ጥራትን በማስጠበቅና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራን ነው ብለዋል።

የቡና አምራችና ላኪ አቶ ፈጠነ የኃላሽት እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በጥራት መጓደል ምክንያት ባመረቱት ልክ ቡናን   ለዓለም ገበያ  እያቀረቡ እንዳልነበር አንስተዋል። 

በአሁኑ ወቅት የቡናን ጥራት ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ የተሻለ ምርትና ጥራት ያለው ቡና ለዓለም እያቀረቡ እንደሆነ ጠቅሰዋል። 

ሌላኛው የቡና አምራች አቶ ሙስጠፋ አወል፤ ከቡና ችግኝ ዝግጅት እስከ ገበያ ያለውን ሂደት በአግባቡ በመጠበቅ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በትብብር መሥራትና የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።


 

ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከአምራቾች ጀምሮ ላኪዎችም የእሴት ሰንሰለቱን ጠብቀው በጥንቃቄ መምራት ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል።

የአባያ ቡና አምራቾች የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አሰፋ በቀለ፤ የቡናን ጥራት ለማስጠበቅ ከአርሶ አደሮች ጀምሮ በግብይት ሂደቱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል

ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ጥራትና ሰርቲፊኬሽን ኃላፊ ብርሃኑ ጋቢሳ፤ ለቡና ምርት ጥራት መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን በመለየት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።



የቡና ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመንግሥት አካላት፣ አምራቾችና ላኪዎች ለምርት ጥራት ማሻሻያ ልዩ ትኩረት በመስጠት በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። 

የቡናውን ምርት ጥራት በማስጠበቅ በተለይም በልዩ ጣዕም ቡና እየተገኘ ያለውን ጥቅም በዘላቂነት ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቡና ምርትና ወጪ ንግድ አፈጻጸም የተሻለ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አርሶአደሮች፣ ላኪዎች፣ ማኅበራትና ክልሎች ባለፈው ሳምንት የእውቅና ሽልማት መስጠታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም