የኢትዮጵያን ስፖርት ከውጤታማነትም ባለፈ የሀገር መልካም ገጽታ ማሳያ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ስፖርት ከውጤታማነትም ባለፈ የሀገር መልካም ገጽታ ማሳያ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያን ስፖርት ከውጤታማነትም ባለፈ የሀገር መልካም ገጽታ ማሳያ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጂራ ገለጹ፡፡
የአህጉሪቷ እግር ኳስ መስራቾች ከነበሩት አገራት መካከል ኢትዮጵያ እንዷ ብትሆንም በዘመናት ጉዞ ውስጥ በእግር ኳሱ የሚጠበቀውን እድገት ማሳየት ተስኗት ቆይቷል።
ለዘርፉ እድገት ማነቆ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል ደግሞ የእግር ኳስ ሜዳ ችግር በዋነኝነት ይጠቀሳል።
በመሆኑም ይህንን የቆየ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በከፍተኛ ጥረትና ተነሳሽነት የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሃሳብ አመንጪነትም ኢትዮጵያ እኤአ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ በማቅረብ የማግባባት ስራዎቿን አጠናክራ ቀጥላለች።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጂራ፤ የኢትዮጵያን ስፖርት ከውጤታማነትም ባለፈ የሀገር መልካም ገጽታ ማሳያ ለማድረግ ከመንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ከ 2017 በጀት አመት ጀምሮ የስፖርት ዲፕሎማሲን ከማጠናከር አኳያ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን በአብነት አንስተዋል፡፡
ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በካፍ አባል አገራት አመራሮችና በቀድሞ የኢትዮጵያ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ ለማካሔድ ቀጠሮ መያዙንም አስታውቀዋል።
የአፍሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ደግሞ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሔድ ጠቁመዋል፡፡
መሰል ጉባዔዎች በአገራት መካከል የባህል ትውውቅና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲፈጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ኢሳያስ ጂራ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ጥያቄ ያቀረበችበት የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ውሳኔ የሚያገኘው በሚቀጥለው አመት ሞሮኮ ላይ በሚካሔደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ደግሞ ኢትዮጵያ በስታዲየም ግንባታ እና እድሳት ዙሪያ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዮና፣ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ጨዋታ፣ የአፍሪካ ጠረንጴዛ ቴኒስ እና አህጉራዊ የእጅ ኳስን ውድድሮችን ማዘጋጀቷ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ያላትን ብቃት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡