የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ በአዲስ አበባ አስቸኳይ ስብሰባውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ በአዲስ አበባ አስቸኳይ ስብሰባውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሂዳል።
ስብሰባው ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ይከናወናል።
ልዩ ቴክኒክ ኮሚቴው ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035 የሚተገበረው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዴፕ) የ10 ዓመት ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር ላይ ውይይት አድርጎ እንደሚያጸድቅ ኢዜአ ከአፍሪካ ሕብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ በመወያየት ደንቡ እንዲፀድቅ በአፍሪካ ሕብረት የፍትሕ እና የሕግ ጉዳዮች ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ እና ለሌሎች የሕብረቱ አደረጃጀቶች እንደሚመራ ገልጿል።
ኮሚቴው በአፍሪካ ሕብረት ስር በሚገኙ የጥናት እና የአሳ ሀብት ልማት ስልጠና፣ በውሃ እና ውሃማ አካላት ላይ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሀብት አጠቃም (Aquaculture) ፣ የውሃ እና ውሃማ አካላት ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እንዲሁም በስነ ምህዳር አስተዳደር ላይ የሚሰሩ የልህቀት ማዕከላት የስራ አፈጻጻም ሪፖርቶችን ያደምጣል።
በተያያዘም የአፍሪካ ሕብረት የስርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ሴቶችን ማብቃት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ዘጠነኛ መደበኛ ስብስባውን በአዲስ አበባ ያደርጋል።
በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሴቶች፣ የስርዓተ-ፆታ እና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀው ስብስባ ከጥቅምት 19 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሕብረቱ አስታውቋል።
ከጥቅምት 19 እስከ 25 የባለሙያዎች እንዲሁም ጥቅምት 26 እና 27 ቀን 2017 ዓ.ም የሚኒስትሮች ስብስባ እንደሚደረግ ተመላክቷል።
30ኛ ዓመቱን ባስቆጠረው ሴቶች እና ልጃገረዶች የስርዓተ-ፆታ እኩልነት እና መብቶቻቸው መከበር ላይ ትኩረቱን ያደረገው የቤጂንግ የመርሆዎች መግለጫ እና የድርጊት መርሃ ግብር አፈጻጸም ላይ ውይይት ይደረጋል።
እ.አ.አ በ2025 በኒው ዮርክ በሚካሄደው 69ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ ኮሚሽን (CSW69) ስብሰባ ላይ የአፍሪካን አቋም የተመለከተ ቅደመ ምክክር እንደሚከናወን ተገልጿል።
የሴቶች ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ የሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ፣ የስርዓተ-ፆታ እኩልነት፣ ፆታዊ ጥቃትን መከላከል በስብስባው ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ናቸው።
የአፍሪካ ሕብረት የስርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ሴቶችን ማብቃት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ከሕብረቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።