ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማስቀጠል የማስተባበር ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ):-በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማስተባበር ሥራ እየተሰራ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር ገለጸ።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠና የማኅበሩ የቦርድ አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ማኅበሩም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማስተባበር ሥራ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ እንዳለው፤ በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በሀገራቸው ብሔራዊ መግባባት፣ ሰላምና ደኅንነት ላይ ሚናቸውን ለመወጣት አጀንዳዎቻቸው ተሰብስቦ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበናል ብሏል።

ኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነቷን በማረጋገጥ በብሔራዊ መግባባት የተፈጠረባት ሀገር እንድትሆን ለማስቻል ሀገራት በስኬት ያካሄዱትን የጠረጴዛ ላይ ምክክርን የመከተል አማራጭ የሌለው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጿል።

ላለፉት 60 ዓመታት ሀገርን ወዳልተገባ መንገድ እያመራት የሚገኘውን የግጭት አዙሪት ለመቋጨትም ሊያመልጥ የማይገባውን የምክክር ዕድል መጠቀም እንደሚገባ ተናግሯል።   

የማኅበሩ የቦርድ አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፤ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ሀገራዊ ምክክሩን በስኬት ማስኬድ ያለን ብቸኛ ዕድል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ማምጣት የሚያስችል የምክክር ምኅዳር በመፍጠር ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረትም የሁሉም ዜጋ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።


 

ሰላም የሁሉ መሠረት መሆኑን የጠቆሙት ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፤ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርም ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።

በቀጣይም ማኅበሩ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን በማስተባበር ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬት የሚያደርጉትን የገንዘብ፣ የሃሳብና ሌሎች ድጋፎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር በውጭ ከሚኖሩና ይኖሩ ከነበሩ ዳያስፖራዎች ያሰባሰበውን አጀንዳና ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የሙዚቃ ክሊፕ (መዝሙር) ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም