የሶማሌ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች ለአገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን ማሰባሰባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሶማሌ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች ለአገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን ማሰባሰባቸው ተገለጸ
ጅግጅጋ ፤ ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ) ፡- የሶማሌ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች ለአገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን ማሰባሰባቸውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ከክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ ተወካዮችም መመረጣቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል ላለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ከ104 ወረዳዎች ከመጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በክልሉ ጅግጅጋ፣ጎዴ እና ዶሎ አዶ ማዕከላት የማህበረሰብ ተወካዮች በ10 የማህበረሰብ ክፍሎች በመደራጀት ለአገር ይጠቅማሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሁሉንም የክልሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት በሚገባ ማሳተፍ መቻሉንም አስረድተዋል።
ተሳታፊዎችም ለአገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳ በተገቢው የማሰባሰብ ተግባራት ማከናወናቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ይህም እንደ አገር የሚያኮራና ኮሚሽኑ ለጀመረው ጥረት ስኬታማነት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን በቀጣይ እሁድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ክልሉን የሚወክለው አጀንዳዎች እንደሚደራጅ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የማህበረሰብ ተወካዮቹ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ 100 የክልሉ ማህበረሰብ ተወካዮች መመረጣቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።