በአቦቦ ወረዳ የሚገኘውን የአልዌሮ ግድብ በሙሉ አቅም ወደ መስኖ እርሻ አገልግሎት ለማስገባት ይሰራል - ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአቦቦ ወረዳ የሚገኘውን የአልዌሮ ግድብ በሙሉ አቅም ወደ መስኖ እርሻ አገልግሎት ለማስገባት ይሰራል - ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ የሚገኘውን የአልዌሮ ግድብ በሙሉ አቅም ወደ መስኖ እርሻ አገልግሎት ለማስገባት እንደሚሰራ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚንስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ገለፁ።
ሚንስትሩ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እና ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ግድቡን ጎብኝተዋል።
የአልዌሮ ግድብ ከ10 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማልማት የሚችል አቅም ቢኖረውም የታቀደለትን ያህል ሳያገለግል መቆየቱን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
በጉብኝቱ ወቅት ሚነስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የታቀደውን አቅድ ለማሳካት የተለያዩ የመስኖ አማራጮችን ተጠቅሞ አመቱን ሙሉ ማምረት ግዴታ ነው ማለታቸውም ተጠቅሷል።
በጋምቤላ ክልል ለረጅም አመታት ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየውን የአልዌሮ ግድብ በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለማስገባት በጥናት ላይ የተመረኮዙ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ክልሉ ሰፋፊ እርሻዎችና ለም መሬት ያሉት በመሆኑ የመስኖ አማራጮችን በማስፋት አመቱን ሙሉ ማምረት ወደሚችልበት አሰራር እንዲሸጋገር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በመሆኑም ግድቡ ተገቢው ጥናት እና እድሳት ተደርጎለት ወደ ስራ እንዲገባ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ መግለጻቸውም ተመላክቷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ያለው የእርሻ መሬትና ውሃ ሀብት በተገቢው መንገድ ለማልማት ማህበረሰቡን እና በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ያሳተፈ የልማት ስራ ይሰራል ብለዋል።
በተለይም አልዌሮን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የተጀመሩ ለመስኖ ስራ አመቺ የሆኑ ወንዞችን በጥናት በመደገፍ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸውም በመረጃው ተመላክቷል።