ቀጥታ፡

የድሬዳዋን ነፃ ንግድ ቀጣና ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን አበርክቶ በሙሉ አቅሙ እንዲወጣ እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 6/2017(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን አበርክቶ በሙሉ አቅሙ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ። 

በኢፌዴሪ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የተመራ አገር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ኮሚቴ የድሬዳዋን ነፃ የንግድ ቀጣና እንቅስቃሴዎች ተመልክቷል።  

በጉብኝቱ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች የፌዴራልና የአስተዳደሩ ከፍተኛ የአመራር አባላት ይገኙበታል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኮርፖሬሽኑ በመላው አገሪቷ ባስገነባቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙ ባለሃብቶች በስራ ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ በነፃ ንግድ ቀጣናና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ስራ የጀመሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ ተኪ ምርት በማምረትና የስራ ዕድል በመፍጠር የጎላ ሚና እያበረከቱ መሆናቸውን በመግለፅ።

በተጨማሪም በየአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

እነዚህን እንቅስቃሴዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለማስገባት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ቡድኑ በነፃ የንግድ ቀጣናው በሚገኘው የለማ መሬት አስፈላጊውን መሠረተ ልማቶች በማሟላት ተጨማሪ አልሚዎችን ለመሳብ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችንም ተመልክተዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከነፃ የንግድ ቀጣናው በተጨማሪም የድሬዳዋን ደረቅ ወደብና ተርሚናል፣ የዘመናዊውን የኢትዮ -ጅቡቲ ምድር ባቡር የድሬዳዋ ጣቢያ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ተመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም