ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባትና ግጭቶችን በማስቀረት ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ፋይዳው የጎላ ነው - የማህበረሰብ ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባትና ግጭቶችን በማስቀረት ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ፋይዳው የጎላ ነው - የማህበረሰብ ተወካዮች
ጅግጅጋ ፤ጥቅምት 6/2016 (ኢዜአ) ፡-ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በማስቀረት ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ በጅግጅጋ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የማህበረሰብ ተወካዮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተሳታፊዎች በጅግጅጋ፣ ጎዴ እና ዶሎ አዶ ከተሞች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በጅግጅጋ ማዕከል እየተከናወነ በሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተገኙት የማህበረሰብ ተወካዮች እንደተናገሩት ሀገራዊ ምክክሩ በህዝቦች መካከል የሚታዩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በማስቀረት ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ፋይዳው የጎላ ነው።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ወይዘሮ ሳፍያ ኢሴ እንዳሉት ከግጭትና አለመግባባት የሚገኘው ትርፍ ጉዳት ብቻ ነው፤ ይህንን ለማስቀረትና ሰላምና አንድነትን ለማጎልበት መመካከርና መወያየት ትልቅ ፋይዳ አለው።
እንደ ወይዘሮ ሳፍያ ገለጻ ሀገራዊ ምክክሩ አንድነትን ለማምጣትና አለመግባባቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አውስተዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል የነበሩና በአሁኑ ወቅትም እየተስተዋሉ የሚገኙ አለመግባባቶችን ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የያዘ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ናቸው።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ ከተለያዩ ዞኖች እንደመምጣታቸው ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም የተለያዩ አጀንዳዎችን በነጻነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ አዱኛ ብርሃኑ በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩ በተለይም በአገሪቷ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ሰላምን የሚያጸና፣ ትልቅ ተስፋም የተጣለበት ነው የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።
በተለይም ከማህበረሰብ ተወካዮች የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በትክክል ፈጻሚው አካል ዘንድ ቀርበው ተግባራዊ የሚደረጉ ከሆነና ኮሚሽኑም እስከመጨረሻው ከሰራ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የህዝቦችን አንድነት ያመጣል ሲሉ ያላቸውን ሃሳብ ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በህዝቦች መካከል የሚታዩ ችግሮችን ነቅሎ በማውጣት አብሮነትና አንድነት እንዲጎለብት የሚያስችል መሆኑንና በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክሩ መድረክ ላይ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሶማሌ ክልል የምክክር መድረክ አስተባባሪ አቶ አወል ሁሴን እንዳሉት፤ በክልሉ በጅግጅጋ፣ ጎዴ እና ዶሎ አዶ ማዕከላት ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እየተካሄደ ነው።
ይህም በ10 የማህበረሰብ የውይይት ቡድኖች ተለይቶ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እያከናወኑ መሆኑና ዛሬ እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል።