የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ሕዝብ ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ሕዝብ ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ):- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ሕዝብ ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጎልበት እንደሚሰራ አስታወቀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከተመድ የምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ሊዲያ ዚጎሞ ጋር ተወያይተዋል።
መንግስት የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ እና ሴቶችን በማብቃት በሁሉም ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል፣ ምላሽ ከመስጠትና ሴቶችን ከማብቃት አኳያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን መከላከልና አፍላ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ከተቋሙ ጋር በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተመድ የምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ሊዲያ ዚጎሞ የኢትዮጵያ መንግስት ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ ላገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተቋሙ ከሚኒስቴሩ የ10 ዓመት የልማት እቅድ እና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር በስርዓታ ጾታ እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአምስት አመት መርሃ ግብር እያዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።
የተቋማቱ ኃላፊዎች አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር እና አቅምን በመገንባት በዘርፉ የተቀመጡ እቅዶችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።