ቀጥታ፡

በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት የዝናብ ስርጭቱ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት የዝናብ ስርጭቱ የሚቀጥል መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት አስታወቀ።

በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በምስራቅ ኢትዮጵያ፣ በኡጋንዳ በርካታ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ሶማሊያ ከመደበኛው በላይ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑንም አስታውቋል።

በደቡብ ምዕራብ ሱዳን፣ በደቡብና መካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍልና በኤርትራ ደቡባዊ ክፍል መጠነኛ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑም ገልጿል።

የታንዛኒያ ሰሜን ምዕራብ እና የኬኒያ ጠረፋማና ምዕራባዊ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ተመሳሳይ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸው አስታውቋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎችና በዩጋንዳ የሰሜንና ደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚጥለውን ከበድ ያለ ዝናብ ተከትሎ ጎርፍ ስለሚኖር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም በመረጃው ተመላክቷል።

በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ከጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊጠነቀቁ እንደሚገባም በመረጃው ተገልጿል።

በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት በኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎችና በሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የዝናብ ስርጭቱ የሚቀጥል በመሆኑ ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ ይጠበቃል ተብሏል።

የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት(ICPAC) በኢጋድ ስር ሆኖ የአየር ትንበያና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን የሚያከናውን ቀጣናዊ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፤ የዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በደቡብ፣ ምስራቅ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው ከቀናት በፊት አስታውቋል።

የክረምት ወቅት ዝናብ እያገኙ በነበሩት በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው ማመላከቱም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም