በአማራ ክልል በቡና ተክል ከለማው መሬት ከ133 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በቡና ተክል ከለማው መሬት ከ133 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል
ባህርዳር ፤ጥቅምት 6/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በቡና ተክል እየለማ ከሚገኘው መሬት ከ133 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በዚህ ዓመት እንደሚሰበሰብ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የድህረ ምርት ባለሙያ አቶ ጌታቸው አዲስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ለዚህም በክልሉ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ ከ361 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዳለ በቅርቡ በተደረገ ጥናት መረጋገጡም ተመላክቷል።
ባለፉት ጊዜያት በተደረገ የተቀናጀ ጥረትም 31 ሺህ 433 ሄክታር መሬት በቡና ተክል ማልማት እንደተቻለ ገልፀዋል።
ከለማው መሬት ውስጥ ከ22 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት የተተከለ ቡና ምርት መስጠት መጀመሩን ገልፀው፤ ከዚህም በዚህ ዓመት 133 ሺህ 550 ኩንታል የተጣራ የቡና ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል ብለዋል።
በቡና ልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከዚህ ወር አጋማሽ ጀምረው የቡና ለቀማ ስራ እንደሚጀምሩም አመልክተዋል።
ለዚህም ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት በመሰብሰብ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አርሶ አደሩ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ለቡና ልማት ተስማሚ በሆኑ 24 ወረዳዎች የቡና ልማት በኩታ ገጠም ተለይቶ የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስገንዝበዋል።
አርሶ አደሩ ቡና የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እየተረዳ በመምጣቱም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከልና ተንከባክቦ በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን አብራርተዋል።
በክልሉ በቡና ልማቱ ተሳታፊ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል በአዊ ዞን የዳንግላ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሙላቱ እንግዳ በበኩላቸው፤ ሩብ ሄክታር በሚጠጋ መሬት የተሻሻሉና ፈጥነው የሚደርሱ የቡና ዝርያዎችን ተክለው በማልማት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።
አርሶ አደሩ በዓመት እስከ ሁለት ኩንታል ጀንፈል ቡና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ጠቅሰው፤ በቀጣይም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል ልማቱን ለማስፋት እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።
''የቡና ምርት በአሁኑ ወቅት ከቤት ፍጆታነት አልፎ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንድንሆን እያደረገ ነው'' ያሉት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን ወረዳ አርሶ አደር አንማው መኮነን ናቸው።
በቡና ተክል እያለሙት ካለው ግማሽ ሄክታር መሬት በዓመት እስከ አራት ኩንታል የተጣራ ምርት ሰብስበው ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።
በያዝነው ዓመትም ካለፈው ዓመት ያላነሰ ምርት ሰብስበው፣ በጥራት አድርቀውና አዘጋጅተው ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።