የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔን ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔን ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፦ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 46ኛው የአፍሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ተጠናቋል።
ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በሁለት ምድቦች አህጉራዊና ቀጣናዊ የእጅ ኳስ ውድድሮች ከጥቅምት 23 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ ተገልጿል።
ጉባዔውንና ውድድሩን በተመለከተ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ከጉባኤው አንድ ቀን አስቀድሞ በአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር አባል አገራት አመራሮችና በቀድሞ የኢትዮጵያ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ እንደሚካሄድ ታውቋል።
በሌላ በኩል በአህጉራዊና ቀጣናዊ የእጅ ኳስ በሁለት ምድቦች አህጉራዊና ቀጣናዊ የእጅ ኳስ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።
በዚሁ አህጉራዊና ቀጣናዊ ውድድር አዋቂና ወጣት ስፖርተኞች ይሳተፋሉ ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔውንና ውድድሩን ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተጠቁሟል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በመግለጫው፤ ጉባዔውና ስፖርታዊ ውድድሩ በኢትዮጵያ መካሔዱ በአፍሪካ አገራት መካከል የባህል ልውውጥ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል።
ሁነቶቹ ለአገራዊ ገጽታ ግንባታና ለስፖርት ዲፕሎማሲ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለጉባዔው ተሳታፊዎችና ለስፖርተኞች በአዲስ አበባ ያሉ የቱሪስት ስፍራዎችንና ታሪካዊ ቦታዎችን ለማስጎብኘት መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
በሁለት ምድቦች አህጉራዊና ቀጣናዊ የእጅ ኳስ ውድድሮች ከጥቅምት 23 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሔድ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትህ ወልደሰንበት ናቸው።
በውድድሩ 12 ቡድኖችና 11 አገራት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው፤ ለጉባዔው ስኬታማነት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት የሚመራ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከመጓጓዣ፣ ከቪዛ፣ ከጤናና ከሆቴል አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በስፋት ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።