የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ምርት ጥራትና ደረጃ ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ምርት ጥራትና ደረጃ ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ምርት ጥራትና ደረጃ ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ በቡና፣ በቅባትና በጥራጥሬ እህል ምርቶች ጥራትና ደረጃ ቁጥጥር፣ የኤሌክትሪክ ግብይትና ጨረታ ላይ ያሰለጠናቸውን 85 ባለሙያዎች አስመርቋል።
ለአራተኛ ጊዜ የተሰጠው ይኸው ሥልጠና ከሁለት ወራት በላይ ጊዜ መውሰዱ ተገልጿል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት ጥራትና ደረጃዎች በመጠበቅ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምርቶች ከሚመረትበት እስከ ግብይት ድረስ ያለውን ሰንሰለት የተሳለጠ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የግብይትና የክፍያ ሥርዓት በማዘመን ምርቶች በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪና ተፈላጊ እንዲሆኑ ለማድረግ የተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር በዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ያለውን የወጪና ገቢ ምርት ጥራትና ደረጃ ይበልጥ ለማስጠበቅ በየደረጃውና በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድማገኘሁ ነገራ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የማዕድን ምርቶች ጥራታቸውንና ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተፈላጊ እንዲሆን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በማሰልጠን የጥራትና ደረጃ ቁጥጥር ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ተከታታይነት ያለው ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሰጠው ሥልጠና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ መሥፈርትን መሠረት አድርገው የጥራትና ደረጃ ቁጥጥርና ክትትል ከማድረግ ባለፈ በዓለም አቀፍ ተቋማት ገብተውና በራሳቸው የሥራ ዕድል ፈጥረው እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።