ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ወደ ፖርት ሱዳን የጀመረው በረራ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ወደ ፖርት ሱዳን የጀመረው አዲስ በረራ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  መስፍን ጣሰው ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ጀምሮ የሱዳን የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ፖርት ሱዳን በየቀኑ የሚደረግ አዲስ በረራ ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፣ በኢትዮጵያ የሱዳን ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሱአድ አሊ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በየጊዜው እያሰፋ መሆኑን በማንሳት በተለይ የአፍሪካ ከተሞችን በአየር ትራንስፖርት በስፋት እያስተሳሰረ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ 61 ከተሞች ላይ የሚበር ሲሆን፤ ዛሬ ወደ ፖርት ሱዳን የተጀመረው በረራ አየር መንገዱ በአፍሪካ ከተሞች ያለውን መዳረሻ ወደ 62 የሚያደርሰው እንደሚሆን ገልፀዋል ።

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ወደ ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሳምንት ሦስት ጊዜ በረራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ በሱዳን ባለው የጸጥታ ችግር ወደ ካርቱም የሚያደርገው በረራ ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም አየር መንገዱ ዛሬ በፖርት ሱዳን የጀመረው በረራ የሁለቱን አገራት ሕዝቦች የቆየ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሚሆን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የአየር ትራንስፖርት ትስስሩ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲሁም ንግድና ቱሪዝምን ይበልጥ እንደሚያሳልጥ ተናግረዋል።

እንዲሁም የሱዳን ሕዝቦች ከፖርት ሱዳን በአዲስ አበባ በኩል ወደ ተቀረው ዓለም መጓጓዝ እንደሚችሉ በመግለጽ፤ ይህ አዲስ የበረራ መስመር ሱዳንን ከአፍሪካና ከመላው ዓለም ጋር ያላትን ትስስር የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።

የፖርት ሱዳን አዲስ በረራም አየር መንገዱ ያሉትን ዓለም አቀፍ መዳረሻ ወደ 140 ከፍ ያደርገዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም አየር መንገዱ አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻ ለማድረግ በዕቅድ ከያዛቸው መካከል  ፖርት ሱዳን  አንዷ መሆኗን ጠቅሰዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም