ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሰላምና መረጋጋት ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው - የአፍሪካ ሕብረት 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሰላምና መረጋጋት ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ። 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሰላምና መረጋጋት ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ። 

የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ጸጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ኃሳብ እየተካሄደ ነው። 

በጉባዔው የተገኙት በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮችና የጸረ-ሽብር ዘርፍ ኃላፊ ባባቱንዴ ባዮሚ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሰላምና ጸጥታ መስፈን እያበረከተች የምትገኘው አስተዋጽዖ የሚደነቅ ነው ብለዋል። 


 

ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ያዘጋጀችው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔም የአህጉሪቷን የተወሳሰቡ የጸጥታ ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ  መሆኑን አንስተው ለኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል።  

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከኮርያ ጀምሮ እስከ ሶማሊያ ድረስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ ተልዕኮዋን  በሚገባ በመወጣት ግንባር ቀደም አገር እንደሚያደርጋት ተናግረዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ፣ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት፣ የታጣቂ ቡድኖችን መጨመርና አሳሳቢውን የምግብ ዋስትና እጦት ምላሽ ለመስጠትም በአፍሪካ አገራት መካከል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል። 

በዓለም ላይ የሚስተዋለው ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት የአፍሪካን ሉዓላዊ መረጋጋት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህም የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር የአህጉሪቷን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የአፍሪካ ሕብረትም ዓለም አቀፍ ትብብሩን በማጠናከር ለአህጉሪቷ ሰላምና መረጋጋት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔም የአፍሪካ ሕብረት በ2063 የጥይት ድምፅ ማስቆም አጀንዳ ተስፋ በማለምለም የአህጉሪቷን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ወሳኝ መድረክ መሆኑን አብራርተዋል። 

በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጀመረው የጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የጉባዔው ተሳታፊ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ወታደራዊ አታሼዎች፣ ወታደራዊ ተመራማሪዎችም የኢትዮጵያ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የለውጥ እርምጃና የልማት ሥራዎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም