ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ በሚገዙበት እና በሚሸጡበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ በሚገዙበት እና በሚሸጡበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳስቧል።

አዲስ የምንዛሪ ተመን አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በውጭ ምንዛሪ ገበያው ላይ ያሉ ሂደቶችን ሲከታተል መቆየቱን የገለፀው ብሔራዊ ባንኩ፤ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ በሚገዙበት እና በሚሸጡበት መካከል ያለው ልዩነት በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

አሁንም ቢሆን ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን ገበያ መር በሆነ መንገድ መተመናቸውን እና ይህንኑ ዋጋቸውን በተናጠል በየቀኑ ማሳወቃቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ብሔራዊ ባንኩ በመግለጫው ጠቁሟል።

ባንኩ እስካሁን በነበረው አሰራር ንግድ ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የሚጠይቁትን ኮሚሽን ከምንዛሪ መሸጫ ጋር ደምረው ያስታውቁ እንደነበር ጠቅሶ፤ ወደፊት ግን ኮሚሽኑን ከምንዛሪ መሸጫ ጋር ሳይሆን በተናጠል ለደንበኞቻቸው እንዲያሳውቁ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም