በገጠር የሚኖሩ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በገጠር የሚኖሩ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017 (ኢዜአ)፡- በገጠር የሚኖሩ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል ኑሯቸውን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዓለም አቀፉ የገጠር ሴቶች ቀን "በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን በትምህርትና በቴክኖሎጂ ተደራሽነት ማብቃት!" በሚል መሪ ኃሳብ በአፍሪካ ኅብረት እየተከበረ ይገኛል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የገጠር ሴቶችን በትምህርትና በቴክኖሎጂ መደገፍና ማብቃት ወሳኝ ነው።
የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት፣ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ችግሮች የገጠር ሴቶችን ከሚፈትኑት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የገጠር ሴቶች የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠማቸው ቢሆንም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
ሴቶች በተሰማሩበት ሙያ ውጤታማ እንዲሆኑ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በማስፋት የገጠር ሴቶችን ሕይወት የማሻሻል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የገጠር ሴቶችን የመሬት ባለቤትና የፋይናንስ ተደራሽ መሆን የሚያስችሉ የሕግና አሠራር ሥርዓቶች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም እንዲሁ።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ሴቶችን በመደገፍ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ አካባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ በበኩላቸው፤ ለአፍሪካ ግብርና የጀርባ አጥንት የሆኑ የገጠር ሴቶችን ማብቃት የጋራ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
የአፍሪካ የገጠር ሴቶችን ሕይወት ለማሻሻል ጥራት ያለው ትምህርትን ማዳረስና ቴክኖሎጂን ማስፋት ለነገ የማይባል መሆኑንም ነው ያነሱት።
የገጠር ሴቶች በግብርናው መስክ ከቤተሰብ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምርት እንዲያመርቱ መደገፍ ይገባል ብለዋል።
ለአህጉሪቱ ዘላቂ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ የገጠር ሴቶች ያላቸውን ሚና እንዲወጡ የኅብረቱ አባል አገራት በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።