ቀጥታ፡

የአፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ትብብር ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ትብብር አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ። 

ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚቆየው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ጊዜ፤ ጉባዔው የአፍሪካን የሰላምና ጸጥታ ትብብር በማጠናከርና አዳዲስ የአጋርነት መንገዶችን በመቀየስ የአህጉሪቷን መፃዒ ዕጣ ፈንታ የተሻለ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ጉባዔው አህጉራዊ የሰላምና ደኅንነት ችግሮችን በመፍታት አስተማማኝና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ለመቅረጽ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።  

ለዚህም ኢትዮጵያ መድረኩን በማዘጋጀቷ ታላቅ ክብር ይሰማታል ነው ያሉት።   

የጉባዔውን አስፈላጊነት በመገንዘብ ከአራቱም የአፍሪካ ማዕዘን የተሰባሰቡ የመከላከያ ሚኒስትርና መኮንኖችም የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የአህጉሪቷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተሻለ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል ነው ያሉት። 


 

ይህ ጉባዔ ስብሰባ ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፤ አፍሪካውያን በሚያጋጥሙን ችግሮች ላይ በጽናት እንድንቆም፣ ሊያደናቅፉን የሚሹትን ሥጋቶችን ለማሸነፍና መፃዒ ዕድሎች የተሻለ በማድረግ የጋራ ፍላጎታችን የምናሳካበት ነው ሲሉ አብራርተዋል። 

አህጉሪቷን እየፈተናት የሚገኘውን የሽብርተኝነት፣  የሽምቅ ውጊያ፣ ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀሎች፣ መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር፣ የሳይበር ጥቃት፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ችግሮችን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አፍሪካዊ ዕውቀትና ልምድ ላይ የተመሠረተ የትብብር አቅምን መገንባትና ማጠናከር ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንዳልሆነም ገልፀዋል። 

በዚህም በጉባዔው ለአህጉሪቷ ሁለንተናዊ የሰላምና ደኅንነት አስፈላጊ በሆኑ ወቅታዊ የጸጥታ ተግዳሮቶች፣ የዓለም ሥርዓትና ተፅዕኖው እንዲሁም በአፍሪካ መከላከያ ኃይሎች ትብብር ላይ ትኩረት ያደረጉ መፍትሔ አመላካች ጉዳዮች ላይ በመመካከር የአፍሪካን የወደፊት የመከላከያ ስትራቴጂ መቅረጽ የሚያስችሉ ርዕሰ- ጉዳዮች ላይ ውይይቶች እንደሚኖሩ ተናግረዋል። 

የጉባዔው ተሳታፊ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ወታደራዊ አታሼዎች፣ ወታደራዊ ተመራማሪዎችም የኢትዮጵያ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የለውጥ እርምጃና የልማት ሥራዎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 

በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጀመረው የጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም