የዲጂታል የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2017(ኢዜአ)፦ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር ከቬክና ቴክኖሎጂና ኦርቢት ሄልዝ ጋር የዲጂታል የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የጋራ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ “ብራት ቦክስ” የተሰኘ ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ በማምረት በገጠር አካባቢዎች ዲጂታላይዝ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ አምራችነት የሚሸጋግር እና አዳዲስ ዕውቀትንና ክህሎትን ለመታጠቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ራስን የመቻል ጉዞ ከማሳካት አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የሥምምነቱ ተግባራዊነት በጤና ቴክኖሎጂ ምርት፣ በሮቦቲክስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማልማት የሚያስችል እድል እንደሚፈጥር ሚኒስትሯ መግለጻቸውን ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።