የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራርና ሠራተኞች ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ፡፡
17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞችም እለቱን ሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና በፓናል ውይይት አክብረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የነፃነት፣ ሉዓላዊነትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተልዕኮ እና ተግባርም ከሰንደቅ ዓላማ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋሙ ሀገራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ፣ ገፅታ በሚገነቡና ብሔራዊ መግባባትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ሀገራዊ ራዕይና የኢዜአ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በውጤታማነት በማከናወን ለሰንደቅ ዓላማው ታማኝ ሊሆኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የትላንት መሰዋዕትነት ውጤት፤ በዛሬ ተጋድሏችን ወደ ነገ የህልማችን ልዕልና መዳረሻ ለሚደረገው ጥረት የአንድነት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ፤ ከትናንት መልካም ነገሮችን ወስደንና ተምረን ነገን ብሩህ ለማድረግ በሰንደቅ ዓላማ ሥር በአንድነት መሰባሰብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከፋፋይ ትርክቶች የሀገርን ሉዓላዊነት የዜጎችን ጥቅምና መብት እየጎዱ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ዓላማ በጋራ የሚያሰባስበን የሉዓላዊነት ምልክት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የሰንደቅ ዓላማን ክብር ለትውልድ ማስተማር እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡