ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት መጠበቅ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን ተፈጻሚነት ለማጠናከር እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ሚዛንን መጠበቅ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን ተፈጻሚነት የሚያጠናክር የድርጊት መርሃ ግብር ወደ ስራ ማስገባቷን አስታወቀች።

በኬንያ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ሶስተኛው የአፍሪካ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ፎረም ተጠናቋል።

በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ43 አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 400 የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ ከንግድ እና ሰብዓዊ መብት ጋር ተዛማጅነት ባላቸው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ጥናታዊ እና መነሻ ጽሁፎች እና ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የንግድ እና ሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ የድርጊት መርሃ ግብርን ለመንደፍ እና ተፈጻሚነቱን ለመከታተል እያደረገች ያለችውን ጥረት አስመልክቶ ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል።


 

በንግድ እና ሰብዓዊ መብት መካከል ያለውን ሚዛን ለማስጠበቅ እና ኃላፊነት የተሞላበትን የንግድ እንቅስቃሴ በተሟላ ሁኔታ እውን ለማድረግ የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር ነድፋ ለመፈጸም እንቅስቃሴ መጀመሯ ተገልጿል።

ኢትየጵያ በመደበኛው የሕግ ማስፈጸም ሂደት በንግድ እና ሰብዓዊ መብት መካከል ያለውን ሚዛን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዳሏት ተመላክቷል።

የሕጎቹን ተፈሚነት በላቀ ሁኔታ ለማጠናከር እና በተናበበና በተቀናጀ ስርዓት ለመምራት የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ነው የተጠቆመው።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፎረሙ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት አድርጓል።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ፎረም አበባ አስተናግዳ እንደነበር ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም