ቀጥታ፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ጀግኖች አባቶች የተዋደቁላትን ኢትዮጵያ በማሰብና አደራቸውን በአግባቡ በመወጣት መሆን አለበት

ቦንጋ ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ጀግኖች አባቶች የተዋደቁላትን ኢትዮጵያ በማሰብና አደራቸውን በአግባቡ በመወጣት መሆን አለበት ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሀሳብ ለ17ኛ ጊዜ በቦንጋ ከተማ በተለያዩ ኩነቶች ተከብሯል።

ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበዓሉ ላይ እንደገለጹት፣ ሰንደቅ ዓላማ የአንድነትና የነጻነት እንዲሁም የአብሮነታችን ማሳያ አርማ ነው።

ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲታይና የሀገሪቱ ሉአላዊነት ተጠብቆ እንዲቆይ ቀደምት አባቶች በደማቅ አሻራ የተጻፈ መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰዋል።

አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አርማችን ከኢትዮጵያ ባለፈ የጥቁር ህዝብች የነፃነት ምልክት መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ቀኑ ሲከበር ጀግኖች አባቶች ያስረከቡንን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነታችንን በተግባር በማሳየት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሁሌም ሰንደቅ ዓላማን ስናከብር የሀገር ክብር፣ ሉአላዊነትና ህብረብሔራዊ አንድነት እያሰበን ሊሆን ይገባል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሁሉም ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብርና ቦታ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።


 

ባለፉት ዓመታት ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር አስተዋጾ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ ናቸው።

በዓሉ በአብሮነት የመቆምና የመጽናት ስሜትን ከመፍጠር ባለፈ ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ክብር የሚያሳድግ መሆኑን አመልክትዋል።

በዓሉ ዘንድሮም ለ17ኛ ጊዜ መከበሩን የገለጹት አቶ ወንድሙ፣ በዓሉ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

በበዓሉ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በብሔራዊ ደረጃ ወጥ በሆነ መልኩ መከበሩ ልዩ ትርጉም እንዳለውና ይህን ለማስቀጠል እንደሚተጉ ተናግረዋል።

ሰንደቅ ዓላማ የማንነታችን መገለጫና ለድርድር የማይቀርብ የሉአላዊነታችን ምልክት ነው ያሉት ኢንስፔክተሩ፣ ዛሬም የጀግኖች አባቶችን ወኔ በመታጠቅ ለሀገር ክብር ጠንክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ለሀገር ሰላም፣ ልማትና አንድነት መጠበቅ ሁሉም በአንድነት መቆም እንዳለበት ጠቁመው፣ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማጽናት በሚሰሩ ሥራዎች የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አርጋገጥዋል። 

"የነጻነታችንና የአንድነታችን ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማችን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ክብራችን ነው" ያሉት ደግሞ ኮማንደር ደረጀ አስፋው ናቸው።  


 

"እጅ ለእጅ ተያይዘን የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ከማስጠበቅ ባለ በየተሰማራንበት ውጤታማ በመሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን ፈተና ማለፍ ይገባናል" ብለዋል። 

በበዓሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ሰንደቅ ዓላማ የመስቀልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የመዘመር ሥነስርአትም በጋራ ተከናውኗል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም