ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የነባርና አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባልነት ምዝገባ እስከ ህዳር 30 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የ2017 የነባርና አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባልነት ምዝገባ ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 እንደሚከናወን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በ2016 የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አፈጻጸም እና 2017 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቢሮው የህብረተሰቡን ጤና አጠባበቅ ለማጎልበት ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዋነኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።

በመዲናዋ በ2016 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓመቱ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ከቀላል እስከ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎቶችን በጤና ጣቢያና በሆስፒታል በቀላሉ ማግኝታቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፥ ይህም ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እያረጋገጠ ነው ብለዋል።


 

በ2017 ዓ.ም የነባር አባላትን እድሳት ለማካሄድና 10 በመቶ የሚሆኑ አዳዲስ አባላትን በመጨመር ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የነባር እና የአዲስ አባላት ምዝገባም ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች መካሄድ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የፀደቀው መደበኛ ዓመታዊ መዋጮ 1 ሺህ 500 ብር መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው የደሃ ደሃ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ወጪውን ከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

ነባር አባላትና አዲስ ተመዝጋቢዎች ለምዝገባ ወደ ጤና ጣቢያዎች ሲያመሩም የመዋጮ 1 ሺህ 500 ብር እንዲሁም የመመዝገቢያ 200 ብር መያዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች እና የቤተሰብ አባላት ያላቸውም በእያንዳንዱ ሰው ተጨማሪ 750 ብር በመክፈል አባል ማድረግ እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

ህብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ካልታሰበ ድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም