ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ብቁ ተቋም ገንብታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ብቁ ተቋም ገንብታለች
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማቶችና በቁልፍ ተቋማት ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችል ብቁ ተቋም መገንባቷን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ገለጹ።
የሳይበር ጥቃት ጉዳይ የመላው ዓለም ስጋት በመሆኑ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሁሉንም ሀገራት ትብብር ይጠይቃልም ብለዋል።
በዱባዩ የጂአይቴክስ መድረክ በተካሄደው የሳይበር ደህንነት ፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግርን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ናት።
በዚህ ሂደት በተቀረው ዓለም እንደሚያጋጥመው ሁሉ በኢትዮጵያ ተቋማት ላይ የተለያዩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።
ጥቃቶችን ለመመከትም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የቅድመ ሳይበር ጥቃት መከላከል ላይ በማተኮር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ዲጅታል መተግበሪያዎችን እና የሳይበር ደህንነትን በተመለከተ ወሳኝ የሕግ ማዕቀፎችን ማውጣቷን ተናግረዋል።
በተለይም በፋይናንስ፤በኃይል እና በተለያዩ መሰረተ ልማት ተቋማት የሳይበር ደህንነት ጥበቃ የሚያደርግ ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማትን በይፋ ወደ ስራ ማስገባቷንም ጠቁመዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም በተለያዩ ጊዜያት የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፍ መቻሉን ነው የገለፁት።
በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትም በትምህርትና ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር በተደረገ ትብብር የ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ስልጠና መጀመሩን ተናግረዋል።
በየዓመቱ ሀገራዊ የሳይበር ወር በሚል ግንዛቤ በሚያስጨብጡ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ጠቅሰዋል።
የሳይበር ደህንነት ፖሊሲም የሰው ኃይል ግንባታን ከግምት ውስጥ ያስገባ ስለመሆኑ ጠቅሰው፥ የሳይበር ደህንነት በመደበኛው ስርዓተ ትምህርት እንዲካተት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዘርፉ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ምሩቃንንም ለማፍራትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጉዳዮችን ቁልፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፥ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ዓለም አቀፋዊ ትብብርን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።