የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ፍቅር ምንጭና የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክታችን ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ፍቅር ምንጭና የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክታችን ነው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ፍቅር ምንጭና የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!" በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ተከብሯል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም ዕለቱን በማስመልከት ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ስርዓት በማካሄድ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረውታል።
በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር ታሪክ፣ ባህል፣ አብሮነትና የወደፊት ተስፋ የሚንጸባረቅበት ወሳኝ አሰባሳቢ ምልክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም የአንድነት ማሳያ፣ የሀገር ፍቅር ምንጭና የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክታችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የአንድነት፣ የዕድገት፣ የተስፋ፣ የሉዓላዊነትና የጀግንነት ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።
ለሀገር ነፃነት ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ ጀግኖች አርበኞች፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የጸጥታና ደኅንነት ተቋም አባላት ተገቢውን ክብር መስጠትም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማክበር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ ጀግኖች ክብር መስጠትም ሰንደቅ ዓላማን ማክበር እንደሆነ አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለማጎናጸፍ በዕውቀትና ክህሎታቸው፣ በኃብትና ልምዳቸው ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እያገለገሉ ላሉ ብርቱ ክንዶች ተገቢውን ክብር መስጠት ማለት እንደሆነ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ቀለማት፣ ቅርጽ፣ ትርጉም፣ አሰቃቀልና አጠቃቀምን በመገንዘብ ለክብሯ ውድ ዋጋ የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ አርበኞችን ማሰብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ክብር መነሻነትም የሀገርን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለሚያንጸባርቁ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር ይኖርብናል ብለዋል።
በጥቅምት ወር የመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮም በፌደራል፣ በክልል፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ተቋማት፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ሥርዓት በማካሄድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር እና ሀገራዊ አንድነትን በሚያትቱ ጣዕመ ዜማዎች ታጅቦ በደማቅ ዝግጅቶች ተከብሯል።