ቀጥታ፡

ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት መገለጫና የህይወት ዋጋ የተከፈለበት በመሆኑ ትውልዱ ሊጠብቀው ይገባል- አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ፤ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ)፡- የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት መገለጫ ለሆነው ሰንደቅ ዓላማ የህይወት ዋጋ መከፈሉን ትውልዱ ተገንዝቦ ተገቢውን ክብር ሊሰጥ ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

17 ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን ፣ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ ተከብሯል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ሰንደቅ ዓላማ የአንድነት ምልክት፣ የሀገር ክብርና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው፡፡

በየዘመናቱ የህይወት ዋጋ የተከፈለበት በመሆኑ ትውልዱ ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገሩ ተገቢውን ክብር ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሃገር በተለያዩ ጊዜያት የገጠማትን ፈተና በህዝቦች አንድነትና ትብብር መቋቋሟን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በርካቶች የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ ለማድረግና ሀገርን ከነክብሯ ለማቆየት የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከርና ብልጽግናን ለማረጋጋጥ የተጀመረውን ጉዞ በማጠናከር መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

በተለይ የአሁኑ ትውልድ ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በጀግንነት የሀገሩን ዳር ድንበር እያስከበረ ላለው መከላከያ ሠራዊት ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሠራዊቱ ምትክ የሌለው ህይወቱን ጭምር ከፍሎ ሀገርና ህዝብን ጠብቆ ማቆየቱን ገልጸዋል።


 

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በበኩላቸው፣ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን ድንጋጌ ተከትሎ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልሉ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን ገልጸዋል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ የሃገር ሉዓላዊነት መገለጫና የኢትዮጵያ ከፍታ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸው፣ በዓሉ ሲከበር ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር በመስጠት መሆን አለበት ብለዋል።

ቀደምት አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ክብሯ ተጠብቆ የቀየችውን ኢትዮጵያ በልማትም ወደፊት ለማምጣት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ፖሊሲ ኮሚሽን አባል ኮማንደር ደጊቱ ጣጊቾ በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ከሀገር የሉዓላዊነት መገለጫ አንዱ ሰንደቅ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ኮማንደር ደጊቱ፣ በተሰማሩበት መስክ የሀገሪቱን ከፍታ የሚያሳድጉ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሰንደቅ ዓላማው ቀን አከባበር ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ቃለ መሃላ ተፈጽመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም