የአሁኑ ትውልድ የምጣኔ ኃብት ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የአሁኑ ትውልድ የምጣኔ ኃብት ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦የአሁኑ ትውልድ በአንድነትና በመተባበር የምጣኔ ኃብት ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።
17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ኃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያውያን የአገር ሉዓላዊነት እንዲከበር፣የሕዝቦችን ነፃነትና ክብር ለማጽናት ለሰንደቅ ዓላማቸው፣ለአገራቸው ፍቅርና ክብር ሲሉ በአንድነት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰዋል።
ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ለሉዓላዊነት የተከፈለ መስዋዕትነትና ሕብረ-ብሔራዊነት የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ገልጸው፤ የአገር ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ፀንቶ የቆየው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ታትሞ የቆየ ብሔራዊ መለያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄ አርማ ምልክት መሆኑንም ገልፀዋል።
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ከትላንት እስከ ዛሬ በደማቸው ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን አስጠብቀው ያኖሯትን አገር የአሁኑ ትውልድ በእውቀቱና በላቡ በማልማት ብልጽግናዋን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ፤ ጠንካራ አገረ-መንግሥት ለመገንባትና የኢትዮጵያን ከፍታ አስተማማኝ መሠረት ላይ ለማስቀመጥ ሁሉም በተሰማራበት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል።
የአሁኑ ትውልድ የራሱ አገራዊ አሻራ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ በአንድ ልብ፣ በአንድ ኃሳብ፣ በራሱ እውቀት ጥረትና ላብ ገንብቶ በማጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንደተወጣ ሁሉ በቀጣይነትም የአገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የትውልዱ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ መልማትና መበልጸግ የምትችል፣ አንጡራ ኃብት ባለቤት፣ ትልቅ ተስፋ ያላት እንዲሁም ብርቱ አገር በመሆኗ የተፈጠሩ ዕድሎችን መጠቀም ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።
ለዚህም የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰለጠነና በሰከነ መንፈስ በንግግር በመፍታት በአንድነት ለእድገትና ብልጽግና በጋራ መቆም እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑ የውስጥና የውጭ ወቅታዊ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት መሻገር የቻለችው በትውልድ ቅብብሎሽ ለአገርና ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ህይወቱን የሚሰጥ በአገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደር ጀግና ትውልድ በማፍራቷ ነው ብለዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር የሚያጋጥሙ የውጭና የውስጥ ፈተናዎችን በተባበረ ክንድ በአሸናፊነት በመሻገር አንድነትና አብሮነትን ለማጽናት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
በመሆኑ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በትውልድ ቅብብሎች ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የኖረችን አገር በምጣኔ ኃብት እድገት ከፍ ለማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4 ሰዓት ተኩል ላይ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በአዋጅ በተደነገገው መሠረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪያው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።