ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ 180 ሀገራትን ያሳተፈው የዓለማችን ግዙፉ የቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁነት በዱባይ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ 180 ሀገራትን ያሳተፈው የዓለማችን ግዙፉ የቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁነት (ጂአይቴክስ ግሎባል 2024) በዱባይ እየተካሄደ ነው።

በዱባይ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል የተከፈተው 'ጂአይቴክስ 2024' በዓለም ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሁነት ከ180 በላይ ሀገራት የተወጣጡ መሪዎች፣ የቴክኖሎጂ አልሚዎች፣ ስታርአፖች እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየተሳተፉ ነው።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፊታችን አርብ የሚካሄደው ግዙፉ የቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁነት ከ6 ሺህ 500 በላይ ኤግዚቪተሮች፣ 200 ሺህ የተለያዩ ኩባንያ መሪዎችን አሰባስቧል።


 

ሁለት መቶ ሺህ ተሳታፊዎችን ባሰባሰበው በዚህ ግዙፍ መድረክ የጎንዮሽ ውይይቶች እየተደረጉ ነው።

በውይይቱ ላይም የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እየተሳተፉ ነው።

በሌላ በኩል አራት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ ኩባንያዎችም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ የራሳቸውን ምርትና አገልግሎት እያስተዋወቁ ነው።

ከእነዚህም መካከል 'አይኢ ሶሉዩሽን' የተሰኘው የአይሲቲ ኩባንያ በሁነቱ ላይ የራሱ ቦታ ገዝቶ ምርት እና አገልግሎቱን እያስተዋወቀ የሚገኝ ብቸኛው ኩባንያ ነው።

ጂአይቴክስ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት በሞሮኮ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም