ለመኖር አስቸጋሪ ከነበረ አካባቢ ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ተሸጋግረናል - የካዛንቺስ እና አካባቢው የልማት ተነሺዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለመኖር አስቸጋሪ ከነበረ አካባቢ ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ተሸጋግረናል - የካዛንቺስ እና አካባቢው የልማት ተነሺዎች

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ለመኖር አስቸጋሪ ከነበረ አካባቢ ወጥተው ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን የካዛንቺስ እና አካባቢው የልማት ተነሺዎች ተናገሩ።
የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ ደረጃዋን የሚመጥን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በአዲስ አበባ በመልሶ ማልማት ላይ ከሚገኙት አካባቢዎች መካከል ካዛንቺስ እና አካባቢው አንዱ ሲሆን፤ ነዋሪዎችም በሌሎች አካባቢዎች መኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው መኖር ጀምረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትላንት ማምሻውን ካዛንቺስ እና አካባቢው ለልማት የተነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች አዲስ ወደገቡበት አቃቂ ገላን ጉራ እና ቦሌ አራብሳ ቤቶች ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል።
አካባቢዎቹ ለተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማትና ፋርማሲ፣የሸማቾች ሱቆች የተሟሉላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለእናቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚውሉ ሼዶች ከውኃ እና መብራት አቅርቦት ጭምር መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በገላን ጉራ መኖሪያ መንደር ያለውን መንገድ ወደ አስፋልት በማሻሻል የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት በፍጥነት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ ማምሻውን ባካሄዱት ጉብኝት ለነዋሪዎች ማዕድ በማጋራትና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማበርከት አብሮነታቸውን ገልፀዋል።
ካዛንቺስ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ ዳንኤል አበበ ለረዥም ጊዜ በአካባቢው እንደኖሩ ተናግረዋል።
በነበሩበት አካባቢ የመጸዳጃ ቤት እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃ ባለመኖሩ ብዙ ችግር እንደነበር ገልፀዋል።
ወደ አዲሱ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡም ወረዳው መልካም አቀባበል እንዳደረገላቸው ገልጸው፤ዕቃቸውን ለማምጣትም ሆነ ለማስወረድ ያለምንም ክፍያ መስተናገዳቸውን ጠቁመዋል።
ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም አቅመ ደካሞች የሚመች ቦታ መሰጠቱ እንዲሁም የማኅበራዊ ህይወት እንዳለ መምጣቱ የሚያስደስት መሆኑን ተናግሯል።
ለልማት ከአካባቢያችን ብንነሳም ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በመረከብ የተሻለ ኑሮ እንድንኖር አድርጎናል ብለዋል።
ሌሎች አስተያየታቸውን ከሰጡን ውስጥ ወይዘሮ ዘውዴ ስለሺ እና ወይዘሮ ትርንጎ ሐረገወይን፤ የነበሩበት ህይወት ለአኗኗርም ይሁን ለጤና አስቸጋሪ እንደነበር ገልፀዋል።
የተሰጣቸው መኖሪያ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረው ምቹ ያልሆነ አካባቢ በማላቀቅ ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ እንዳሸጋገራቸው ተናግረዋል።
መንግሥት በዚህ መልኩ ላደረገላቸው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
ከአስከፊ ህይወት ተላቅቄ ያላሰብኩትን ዕድል አግኝቻለው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ድሪባ በዳዳ ናቸው።
አሁን ላይ የተሻለ ቤት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ምንም ቅር የሚያሰኝ ነገር እንደሌለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።