ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ88 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ88 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ88 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለፀ።
ኮሚሽኑ የ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ ኮሚሽኑ 87 ነጥብ 21 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 88 ነጥብ 01 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ችሏል።
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 38 ቢሊየን 151 ሚሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ከተያዘው ዕቅድ 100 ነጥብ 8 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ኮንትሮባንድን ከመከላከል ጋር በተያያዘም በድምሩ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚገመት ልዩ ልዩ ንብረት በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ገልፀዋል።
በኮንትሮባንድ ቁጥጥር ሥራ የተያዙትም የቁም እንስሳት፣ ጨርቃጨርቅና ሌሎች ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት።
ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የጠቀሱት።
ከአጠቃላይ ገቢው ውስጥ 50 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ከሰነድ ምርመራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም የተገኘ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ይህ ትልቅ ስኬት ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻል የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ውጤቱ የመጣው ከኮሚሽኑ አመራር ጀምሮ ሁሉም ሠራተኛ በነበራቸው ቅንጅታዊ አሠራር መሆኑንም አስታውቀዋል።