ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የፓርላማ ኅብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ)፦ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 149ኛው ዓለም አቀፍ የፓርላማ ኅብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

ህብረቱ በዚህ ጉባኤው በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን፣ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ዙሪያ እና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ማጎልበት በሚሉ ዋና ዋና ርዕሶች ዙሪያ በመምከር ዉሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች መፍትሄ ለማመላከት እና በፓርላማ ደረጃ ሊተገበሩ የሚችሉ የትብብር መፍትሄዎችን ለመፈተሽ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያም ይመክራል ተብሏል።


 

የኢትዮጵያ ተሳትፎ አገሪቱ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ትብብሯን ይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በቆይታዉ በዘርፋ የአገራችንን ልምድ በተመለከተ ተሞክሮውን እንደሚያካፍልም ተጠቅሷል።

የአለም አቀፋ የፓርላማ ህብረት ጉባኤ በዓለም ዙሪያ ላሉ የፓርላማ አባላት ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመወያየት እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር መድረክ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም