የክልሉ ህዝብ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማፋጠን የድርሻውን መወጣት አለበት - አቶ አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ህዝብ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማፋጠን የድርሻውን መወጣት አለበት - አቶ አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፡- የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማፋጠን ተግቶ በመስራት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ተናገሩ።
“ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳበ 17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለአፍሪካውያን ጭምር የነፃነት ምልክት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችንና የሉዓላዊነታችን፣ የህዝቦች የነፃነትና አብሮነት መገለጫ ነው ብለዋል።
የህብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ ዓርማችን በመሆኑ ቀጣዩ ትውልድ ሊያከብረውና ሊጠብቀው ይገባል ሰሉም አመልክተዋል።
የክልሉ ህዝብ ለሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ሞገስ መስጠቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ ከመንግስት ጎን ሆኖ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማቱን ለማፋጠን የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን ምሰሶ፣ የአይበገሬነት መገለጫና የብዝሃነታችን መተሳሰሪያ ገመድ ነው ብለዋል።
ይህም በትውልዶች መስዋዕትነት ያስጠበቅነው የነፃነታችን ምልክት መሆኑን በመረዳት ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር መስጠት አለብን ነው ያሉት።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ዕለቱን ስናከብርም ጀግኖች አባቶቻችንንና እናቶቻችንን በማስታወስ ነው ብለዋል።
ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማፅናት ገናና ታሪካችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ቃላችንን የምናድስበትና ለአዲሱ ትውልድ አደራ የምናስተላልፍበት ዕለት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ያስመዘገብናቸው ድሎችን አጠናክረን በማስቀጠልና ያሉብንን ፈተናዎች በመሻገር የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው ርብርብ ቃላችንን ወደ ተግባር መለወጥ ይጠበቅብናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።