ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄ አርማ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ታትሞ የቆየ ብሔራዊ መለያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የነፃነትና የእኩልነት የንቅናቄ አርማ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተናገሩ።

17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ኃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል።


 

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያውያን የሀገር ሉዓላዊነት እንዲከበር፣ የሕዝቦችን ነፃነትና ክብር ለማጽናት ለሰንደቅ ዓላማቸው፣ ለሀገራቸው ፍቅርና ክብር ሲሉ በአንድነት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰዋል።

ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ለሉዓላዊነት የተከፈለ መስዋዕትነትና ሕብረ-ብሔራዊነት የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ፀንቶ የቆየው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ሲሉም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ታትሞ የቆየ ብሔራዊ መለያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄ አርማ ምልክት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎችና አባላት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረትን ጨምሮ አባት አርበኞች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎችና በኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ላይ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በአዋጅ በተደነገገው መሠረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪያው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም