ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለልማት የተነሱ ነዋሪዎች አዲስ የገቡበትን አቃቂ ገላን ጉራ እና ቦሌ አራብሳ ቤቶች ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትላንት ማምሻውን ለልማት የተነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች አዲስ ወደ ገቡበት አቃቂ ገላን ጉራ እና ቦሌ አራብሳ ቤቶችን መጎብኘታቸውን ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከዚህ ቀደም ከነዋሪዎቻችን ጋር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

በውይይት መድረኮቹ ላይ በመግባባት በጋራ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ተነሺ ነዋሪዎችን አዲስ የገቡባቸው አካባቢዎች ለኑሮ የሚስማሙ ጥሩ አየር፣ የጋራ መጠቀሚያዎች ያላቸውና ንጹህ፣ ጽዱና ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች የተሟሉላቸው የመኖሪያ ቤቶችን ያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አካበቢዎቹ ለተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማትና ፋርማሲ፣ የሸማቾች ሱቆች የተሟሉላቸው ናቸውም ብለዋል።

በተጨማሪም ለእናቶች እና ወጣቶች የስራ እድል የሚውሉ ሼዶች ከውሃ እና መብራት አቅርቦት ጭምር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በገላን ጉራ መኖሪያ መንደር እስከ መንደሩ ድረስ የሚዘልቀውን የመንገድ ደረጃ ወደ አስፋልት በማሻሻል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በፍጥነት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።

እንዲሁም የተማሪዎች የክፍል ጥበት በማጋጠሙ በ2 ወር የሚጠናቀቅ ትምህርት ቤት፣ የልጆች መጫዎችን ግንባታ እና የእንጀራ ማምረቻ ማእከልም አስጀምረናል ነው ያሉት።


 

ከንቲባዋ ማምሻውን ባካሄዱት የቤት ለንቦሳ ጉብኝት መርሃ ግብር ለነዋሪዎች ማዕድ በማጋራት እና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማበርከት አብሮነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የምንሰራው ለሀገራችን ብልፅግና ሲሆን የሀገራችን ብልፅግና ደግሞ የዛሬ እና የነገዉን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

በፍትሃዊነት እንሰራለን፤ ጊዜያዊ ችግሮችን ጨከንብለን በትብብር ሰርተን በፍጥነት እናልፋቸዋለን ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ ካልሆነ ለውጥ አይኖርም ያሉት ከንቲባዋ ለውጥ ካላመጣን ደግሞ ጉስቅልና ይቀጥላል ነው ያሉት።

ትጋታችን ከልማታችን ተቋዳሽ ሳይሆን ማንም ወደኋላ እንዳይቀር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ለከተማችን ልማት በሙሉ ልባችሁ ትብብር አድርጋችሁ የከተማውን የልማት ስትራቴጂ የደገፋችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ለተዛባ መረጃ ቦታ ሳትሰጡ ከጎናችን ሆናችሁ ስላበረታታችሁን በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ያለኝን አክብሮት እየገለጽኩ ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም