ቀጥታ፡

የሉዓላዊነትና የነጻነታችን ዓርማ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እንጠብቀዋለን -ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን ዓርማ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እንጠብቀዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ኃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤልን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት በተገኙበት ቀኑን አክብሯል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በዚሁ ጊዜ፤ ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት ምልክት፣ የነፃነት ዓርማና የክብር መገለጫ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን ሰንደቅ ዓላማ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እንጠብቀዋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለሀገር፣ ለህዝብና ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ሁሌም መስዋዕትነት እንደሚከፍልም ገልጸዋል።

ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ክብር ከመሆኑም ባሻገር ለአፍሪካውያን የነጻነት አርማ መሆኑን ተናግረዋል።

ፌደራል ፖሊስ በማደግና በመበልጸግ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ዕድገቷ እንዲፋጠንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሁሌም ዝግጁ ነው ብለዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሀገራችንን በጀግንነት እየጠበቅን በሰብዓዊነት ሕዝባችንን እያገለገልን የምናከብረው በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም