ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በሀረሪ ክልል ተከበረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል 17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በተገኙበት ተከብሯል።

በመርሃ-ግብሩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም እንዳሉት ሰንደቅ አላማ ቀንን ስናከብር አንድነትን በማጎልበት ሊሆን ይገባል።

በመሆኑም የሰንደቅ አላማ ቀንን ስናከብር አንድነትን እና ልማትን ይበልጥ በማጎልበት፤ ጠንክረን በመስራት ድህነትን ታሪክ በማድረግ ሰንደቅ አላማችን በአለም ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲታይ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው ሰንደቅ አላማ የአንድነት መገለጫ እና ታሪካዊ ትስስራችን የሚንፀባረቅበት መሆኑን መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በመርሃ ግብሩም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም፣ የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተቋማት ሰራተኞች፣ የፀጥታ አካላት እንዲሁም የክልሉ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም