ሰንደቅ ዓላማችን የጀግንነታችን ምልክት ነው - ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማችን የጀግንነታችን ምልክት ነው - ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ ሰንደቅ ዓላማችን የጀግንነታችን ምልክት ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ።
17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።
በዓሉ በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ ቅጥር ግቢ የተከበረ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ባስተላለፉት መልዕክት ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነት አርማችን ነው ብለዋል።
ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ሰንደቅ ዓላማችን በተውለበለበበት ቦታ ሁሉ ሰላም አለ፤ ነፃነት አለ ብለዋል።
ለመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የወኔያችንና የጀግንነታችን ምልክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በዓሉ በድጋሚ ለሀገር እና ለህገመንግስታችን ዘብ ለመቆም ቃላችንን የምናድስበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።